Global Good News Literature

Amh_mkbl.jpg (142585 bytes)

 

divider1.gif (1097 bytes)

If you cannot read the Amharic font below, you need an Amharic Unicode Font in order to read this booklet.   

Anyone can use this booklet for personal study,  one-to-one descipleship, or group descipleship.  It can be printed and distributed as long as it is distributed freely.

divider1.gif (1097 bytes)

ማውጫ

   I      ክርስቶስን መቀበል

1. ክርስቶስን መቀበል ምን ማለት ነው@

2. ኢየሱስ ክርስቶስን ስንቀበል በሕይወታችን ምን ለውጥ ሆነ@

3.  አንድ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንደሚገባ እርግጠኛ መሆን ይችላል@

 

     II.      በክርስቶስ ማደግ

 

1. ጸሎት

2. የእግዚብሔር ቃል

3. ከአማኞች ጋር ሕብረት ማድረግ

 

     III      ለክርስቶስ መኖር

1. ለክርስቶስ የምንኖረው እንዴት ነው@

2. ምስክርነት ምን ማለት ነው@

 

ክርስቶስን መቀበል

1. ክርስቶስን መቀበል ምን ማለት ነው@

‹‹(ኢየሱስ ክርስቶስን) ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት የእግዚአብሔር ልጆ ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፡፡›› ዮሐ. 1$12

      ከዚህ ጥቅስ እንደምንመለከተው ኢየሱስ ክርስቶስን መቀበል የሚለው ቃል ከእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የወጣ እንጂ ሰዎች የፈጠሩት አነጋገር አይደለም፡፡ ክርስቶስን መቀበል ሲባል በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን ግራ እንጋባለን፣ በህፃንነታችን ክርስትና የተነሣን ስለሆንን፤ እኔ ከህፃንነቴ ጀምሮ ክርስቲያን ነኝ፤ ክርስቶስን ተቀበል የምትሉኝ እንዴት ነው የሚል ጥያቄ በአእምሮአችን ይመጣል፡፡

ከሕፃንነቴ ጀምሮ ክርስቲያን ነኝ@

      ክርስትናም ሆነ ማንኛውም ዓይነት እምነት አንድ ሰው ካደገ በኋላ አመዛዝኖ የሚቀበለው እንጂ እንደ ቤትና ርስት በውርስ የምናገኘው ነገር አይደለም፡፡ አባትየው ዶክተር ስለሆነ ልጁም ዶክተር ሆኖ እንደማይወለድ ሁሉ፤ እናትና አባቶቻችን ክርስቲያኖች ስለሆኑ እኛም ክርስትናን ወርሰን መወለድ አንችልም፡፡ የእነርሱ እምነት ለእኛ መልካም አርአያ ሆኖልናል፤ በፊሪሃ እግዚአብሔር እንድናድግ ሊረዳን ይችላል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው የእግዚአብሔር ቃል በሚለው መሠረት ክርስቲያን መሆን የሚችለው፤

1.     ኃጢአተኛ መሆኑን ሲገነዘብ፤

‹‹ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል›› ሮሜ 3$23

2.     ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ኃጢአቱ ሲል እንደሞተ ሲያምን፤

‹‹ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፡፡›› ሮሜ 5$8

3.     እስከ ዛሬ የሠራሁትን ኃጢአት ሁሉ ይቅር በለኝ ብሎ ከልብ ንሥሐ ሲገባና ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወቱ ጌታና አዳኝ አድርጎ ሲቀበል፡፡

 ‹‹እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንሥሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፡፡›› ሐዋ. 17$30

        ‹‹የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻል፡፡›› 1ዮሐ. 1$7

        ‹‹እነሆ በልባችሁ ደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ በሩንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ፡፡›› ራእ. 3$20

‹‹ይህንን ተገንዘበው ከዚህ በፊት ክርስቶስን ለመቀበል ውሳኔ አላደረጉ እንደሆን ይህንን አጭር ጸሎት ከልብ ይጸልዩ››፡፡

‹‹ጌታ ሆይ፤ ኃጢያተኛ እንደሆንኩኝ አውቃለሁ፡፡ የክርስትናን እምነት በውርስ ማግኘት እንደማይቻልም ተረድቻለሁ፡፡ ከተወለድኩ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ የሠራሁትን ኃጢአት ሁሉ ይቅር በለኝ፡፡ ለእኔ ስትል ባፈሰስከው ደም እጠበኝ፡፡ ወደ ልቤ እንድትገባ የልቤን በር እከፍትልሃሁ፡፡ ና! ወደ ልቤ ግባ፤ የሕይወቴም አዳኝና ጌታ ሁን፡፡ ስለሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ አሜን››

መቀበል ስንል ምንን ያመለክታል@

መቀበል የሚለው ቃል አንድ የተሰጠ ነገር መኖሩን ያመለክታል፡፡ ሰጭ ከሌለ ተቀባይም ሊኖር አይችልም፡፡ ክርስቶስን መቀበል ስንልም ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር አብ ለዓለም ሁሉ የተሰጠ ስጦታ እንደሆነ ያሳያል፡፡ በእርሱ (በኢየሱስ ክርስቶስ) የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን (ኢየሱስ ክርስቶስን) እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን (ሰዎችን) እንዲሁ ወዷልና፡፡ ዮሐ 3$16

   ከዚህ ጥቅስ እንደምንመለከተው ኢየሱስ ክርስቶስ እንድንበት ዘንድ ለዓለም ሁሉ የተሰጠ የነጻ ስጦታ ነው፡፡

   የእግዚአብሔር ቃል ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀበሉ በሚልበት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ለኃጢአታችሁ መሥዋዕት ይሆን ዘንድ የተሠጣችሁ የዓለም መድኃኒት (መድኃኒዓለምን) ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ልባችሁ ተቀበሉት ማለቱ ነው፡፡

   አንድን መድኃኒት በእጃችን ይዘን ይህ መድኃኒት እንደሚፈውሰኝ አምናለሁ ብንል፤ በመጠጣት፤ በመዋጥ፤ ወይም በመርፌ ያንን መድኃኒት ከደማችን ጋር ካላዋሃድነው ሊፈውሰን አይችልም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስንም ወደ ልባችን ተቀብለን የሕይወታችን ጌታ ካላደረግነው ስለ ኢየሱስ ማወቃችን ወይም መስማታችን ብቻ ከዘላለም ጥፋት አያድነንም፡፡

 

2. ኢየሱስ ክርስቶስን ስንቀበል በሕይወታችን ምን ለውጥ ሆነ@

1. የእግዚአብሔር ልጆች ሆንን፤

ለተቀበሉት ሁሉ በስሙ ለሚያምኑት የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፡፡ ዮሐ. 1$12

በዚህ ጥቅስ መሠረት ሰዎች ሁሉ በጅምላ የእግዚአብሔር ልጆች እንዳልሆኑ እንረዳለን፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ሕይወታችን በንሥሐና በእውነተኛ ልብ መቀበል አለብን፡፡

2. በመንፈስ ዳግም ተወለድን፤

   እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም፡፡ ዮሐ. 3$5

 እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን፡፡  ቲቶ 3$5

3. በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ሆንን፤

ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኖአል፡፡ 2ቆሮ. 5$17 

   4. ከጨለማ ወደ ብርሃን ወጣን፤

እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን (የክርስቶስን) በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ የንጉሥ ካህናት፤ ቅዱስ ሕዝብ፤ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፡፡ 1ጴጥ. 2$9

   5.  የእግዚአብሔር ወገን ሆንን፤

እናንተ ቀድሞ ወገን አልነበራችሁም አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ፤ እናንተ ምሕረት ያገኛችሁ አልነበራችሁም አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል፡፡ 1ጴጥ. 2$10

6.        ከመንፈሳዊ ሞት ወደ ዘላለማዊ ሕይወት ተሸጋገርን፤

    በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን (በመንፈስ) ነበራችሁ... ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለጠጋ ስለሆነ፤ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፡፡ ኤፌ. 2$1፤ 4-5፡፡

    እውነት እውነት እላችኋላሁ፤ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፡፡

 

3. አንድ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንደሚገባ እርግጠኛ መሆን ይችላል@

የእግዚአብሔር ቃል በ1ዮሐ. 5$13 ‹‹የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም (በኢየሱስ ክርስቶስ) ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ፡፡›› በማለት የዘላለም ሕይወት እንዳለን ማወቅ እንደምንችልና ማወቅ እንዳለብንም ያሳስበናል፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ድብብቆሽ አይጫወትም፤ ማወቅ የሚገባንን ሁሉ በቃሉ ገልጾልናል፡፡

‹‹ልጁ (ኢየሱስ ክርስቶስ) ያለው ሕይወት (የዘላለም ሕይወት) አለው ልጁ የሌለው ሕይወት የለውም፡፡›› 1ዮሐ. 5$12

በዚህ ቃል መሠረት ሰዎች ሁሉ በሁለት ይከፈላሉ፤ የዘላለም ሕይወት ያላቸውና የዘላለም ሕይወት የሌላቸው፡፡ ይህንንም የሚወስነው ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወታችን መኖሩና አለመኖሩ ነው፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወታችን ውስጥ ካለ የእግዚአብሔር መንፈስ፤ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ወይም የዘላለም ሕይወት እንዳለን ለመንፈሳችን እንደሚመሰክርልን የእግዚአብሔር ቃል ያስረዳል፡፡

‹‹የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ (መንፈስ ቅዱስ) እርሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል፡፡ ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለትም የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፡፡›› ሮሜ 8$16

 

በክርስቶስ ማደግ

 

‹‹እንግዲህ ክርስቶስ ኢየሱስን እንደተቀበላችሁ በእርሱ ተመላለሱ፤ ሥር ሰዳችሁም በእርሱ ታነጹ፤ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፤ ምሥጋና ይብዛላችሁ፡፡››

ክርስቶስን መቀበል ወይም መዳን የክርስትና ሕይወት ጅማሬ ነው እንጂ ፍጻሜው አይደለም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ከተቀበልን በኋላ በእርሱ ማደግ አለብን፡፡ በእርሱ ሥር መስደድ አለብን፡፡

በክርስትና ሕይወታችን ከህፃንነት ወደ ልጅነት፤ ከልጅነት ወደ ጎልማሳነት፤ ከጎልማሳነት ሙሉ ሰው ወደ መሆን እያደን መሄድ አለብን፡፡

‹‹ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፤ እንደ ልጅም አስብ ነበር፤ እንደ ልጅም እቆጥር ነበር፤ ጎልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ፀባይ ሽሬአለሁ፡፡›› 1ቆሮ. 13$11፡፡

እድገት ጊዜ የሚወስድ ሂደት (Process) ነው፡፡ ቶሎ የሚያድግ ነገር፤ ቢኖር አረምና ሣር ብቻ ነው፡፡ ፍሬ ያለው፤ ለሰዎችም የሚጠቅም ዛፍና ተክል ሁሉ ለማደግ ጊዜ ይወስዳል፡፡  ለማደግ የሚያስፈልጉትን ነገሮችም፤ ማለትም አየር፤ ምግብ (ውሃና አንዳንድ ንጥረ ነገሮች)፤ የፀሐይንም ብርሃን በየጊዜው ማግኘት አለብን፡፡

አንድ በመንፈስ ዳግም የተወለደ ሰውም ጤናማ ሆኖ ለማደግ የሚያስፈልጉት የተለያዩ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህን ነገሮች በየጊዜው ካላገኘ ዕድሜ ልኩን መንፈሳዊ ህፃን ይሆናል፡፡ ወይም እድገቱ ጤናማ አይሆንም፡፡

 

ለአንድ ክርስቲያን ዕድገት የሚያስፈልጉት ነገሮች ምንድን ናቸው@

ለአንድ ተክል ዕድገት ከላይ የተጠቀሱት ሦስት የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ፤ ለአንድ ክርስቲያንም ዕድገት የሚያስፈልጉ ሦስት መሠረታዊ ነገሮች አሉ፡፡

እነዚህም፤ 1ኛ ጸሎት

          2ኛ የእግዚአብሔር ቃል

          3ኛ የአማኞች ኅብረት ናቸው፡፡

1. ጸሎት

ጸሎት ለአንድ ክርስቲያን ዕድገት ከሚያስፈልጉት ነገሮች ዋነኛው ነው፡፡ ለአንድ ተክል ዕድገት አየር እንደሚያስፈልገው ሁሉ የአንድ ክርስቲያን አየር ወይም ትንፋሽ ጸሎት ነው፡፡ አንድ ሰው ሳይተነፍስ ብዙ መቆየት አይችልም፡፡ አንድ ክርስቲያንም መጸለይ ካቆመ መንፈሳዊ ትንፋሽ እያጠረው ይሄዳል፤ ይዝላል፤ ይጠወልጋል በኋላም ከጌታ እየራቀ ወደ ድሮ ሕይወቱ ይመለሳል ስንተነፍስ የተቃጠለውን አየር ወደ ውጭ፤ አዲስን አየር ደግሞ ወደ ውስጥ እንደምናስገባ፤ ስንጸልይም ኃጢአታችንንና ድካማችንን በንሥሓ ጸሎት ወደ ውጭ አስወጥተን አዲስ ጸጋንና ምሕረትን ደግሞ ወደ ውስጥ የምንቀበልበት መንገድ ነው፡፡

 

ሀ. ጸሎት ምንድን ነው@

ጸሎት፤ አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር በመንፈሱ ግንኙነት ሲያደርግ ማለት ነው፡፡ የልቡን ሐዘን ሆነ ደስታ፤ ምሥጋናም ሆነ የሆድ ብሶት፤ ልመናም ሆነ አምልኮ ለእግዚአብሔር ሲያስታውቅና እግዚአብሔር ደግሞ ለልቡ የሚናገረውን ሲያዳምጥ ነው፡፡ ትክክለኛ ጸሎት ለእግዚአብሔር መናገር ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ለልባችን የሚናገረንንም መስማት ያጠቃልላል፡፡ በጽሞና ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል ስናነብ ይናገረናል ወይንም በቀጥታ ለልባችን ይናገረናል፡፡ (አሞ. 4$13)

በአጠቃላይ ጸሎት ማለት ከሰማያዊው አባታችን ጋር በየጊዜው መነጋገር ማለት ነው፡፡ ከአባቱ ጋር የማይነጋገር ልጅ ችግር አለበት፡፡ ከእግዚአብሔርም ጋር በየጊዜው የማንነጋገር ከሆነ አንድ ማስተካከል ያለብን ነገር አለ ማለት ነው፡፡

ለ. የተለያዩ የጸሎት ዓይነቶች አሉ

1. የንሥሐ ጸሎት

ይህ የጸሎት ዓይነት ከሌሎቹ የጸሎት ዓይነቶች ሁሉ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነው ምክንያቱም ኃጢአት በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን ግንኙነት ስለሚያቋርጥ ቶሎ ብለን የተቋረጠውን ግንኙነት በንሥሐ ማስተካከል አለብን፡፡

‹‹እነሆ የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፤ ጆሮውም ከመስማት አልደነቆረችም፤ ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፤ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል፡፡››  ኢሳ. 59$1-2

በተለይ ኅሊናችን በግልጽ የሚወቅሰን ኃጢአት ካለ ቶሎ በንሥሐ ከእግዚአብሔር ይቅርታን መቀበል አለብን፡፡

‹‹በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነፃን የታመነና ጻድቅ ነው፡፡›› 1ዮሐ. 1$9

      ልጆቼ ሆይ፤ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ፡፡ ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ 1ዮሐ. 1$7፤ 2$1

የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል፡፡

ኅሊናችንን የሚወቅሰን ነገር ከሌለ ግን ለጸሎት በተንበረከክን ቊጥር የንሥሐ ጸሎት መጸለይ የለብንም፡፡ ‹‹ወዳጆች ሆይ ልባችንስ ባይፈርድብን በእግዚአብሔር ዘንድ ድፍረት አለን፡፡›› 1ዮሐ. 3$21

አንዳንድ ጊዜ ግን ከእኛ የተሰወረ ኃጢአት ሊኖር ስለሚችል እንደ ዳዊት

‹‹ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ›› ማለት ይኖርብናል፡፡ መዝ. 19$12

2. የልመና ጸሎት

ይህ ጸሎት፤ የሚያስፈልገንን ነገሮች ከእግዚአብሔር የምንለምንበት ጸሎት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ‹‹ለምኑ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ ይከፈትላችሁማል፡፡ የሚለምን ሁሉ ይቀበላል›› ማቴ. 7$7-8 ባለው መሠረት የሚያስፈልገንን ነገር ለመለመን የልጅነት መብት ተሰጥቶናል፡፡

ይህ ጸሎት የሚያስጨንቀንን ነገር ሁሉ በእርሱ ላይ የምንጥልበት ጸሎት ነው፡፡

‹‹በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምሥጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ፡፡›› ፊልጵ. 4$6

‹‹እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት፡፡›› 1ጴጥ. 5$7

ለዚህ ለልምና ጸሎት ከእግዚአብሔር ሦስት ዓይነት መልሶችን ማግኘት እንችላለን፡፡

ሀ. እሺ- የለመንነው ነገር ለሕይወታችን አስፈላጊና እግዚአብሔርን የሚያስከብር ከሆነ እሺ ብሎ ልመናችንን ይሰጠናል፡፡

እግዚአብሔር በቅንነት የሚሄዱትን ከመልካም ነገር አያሳጣቸውም፡፡ መዝ. 84$11

እግዚአብሔር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝም የለም፡፡ መዝ. 23$1

ለ. ቆይ የለመንነው ነገር ለሕይወታችን የሚያስፈልግና ለእግዚአብሔር ክብር የሚሆን ቢሆንም፤ የእግዚአብሔር ጊዜ ከእኛ ጊዜ ስለሚለይ ቆይ የሚለን ጊዜ አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከለመንነው ነገር ይልቅ ይበልጥ የሚያስፈልገን ትዕግሥት ስለሆነ መልሱ ይዘገያል፡፡ አንዳንድ ጊዜ እምነታችን እንዲያድግ ስለሚፈልግ ባሰብነው ጊዜ አይሰጠንም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ያንን የለመንነውን ነገር ለመቀበል ገና ስለሆንን እኛ እስከምሠራና ("ን" ጠበቅ ብሎ ይብ) እስከምንዘጋጅ መልሱ ይቆያል፡፡

በአጠቃላይ ጠቢቡ ሰሎሞን፤ ለሁሉ ‹‹ዘመን (ጊዜ) አለው፤ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው፡፡›› (መክ. 3$1) ብሎ እንደተናገረው የልመናችን መልስ የተመደበለትን የእግዚአብሔርን ጊዜ መጠበቅ ይኖርበታል፡፡

ሐ. እምቢ፤ ልጆ የሚለምኑትን ልመና ሁሉ እሺ የሚል ምድራዊ አባት አለ ማለት ያስቸግራል፤ ካለ ትንሽ የአእምሮ ቀውስ አለበት ማለት ነው፡፡ የሰማዩ አባታችን፤ እግዚአብሔርም ሳናውቅ ባለማስተዋል የምንለምነውን ልመና እምቢ ይለናል፡፡ ማታ. 20$20-22

 

የእግዚአብሔር ቃል እንደሚለው ሰዎች ከእግዚአብሔር የማይቀበሉበት ምክንያቶች ሦስት ናቸው፡፡

1. ስለማንለምን፤ ‹‹አትለምኑምና አታገኙም›› ያዕ. 4$2

2. የምንለምነው ነገር እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ካልሆነ ያዕ. 4$3፤ 1ዮሐ. 5$14-15

3. በልባችን ኃጢአት ሲኖር፤ ‹‹በልቤስ በደልን አይቼ ብሆን ጌታ አይሰማኝም ነበር፡፡›› መዝ. 65(66)፡18

 

3. የምልጃ ጸሎት

ለራሳችን ሳይሆን ለሌሎች መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ችግር የምንጸልየው ጸሎት ነው፡፡

ሀ. እኛ ራሳችን ለእከሌ ልጸልይ ብለን የምንፈጸልየው ጸሎት፡፡

‹‹በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምሥጋና ጋር ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ፡፡›› ፊል. 4$6

በአንድ ሰው ሕይወት ድካም ስናይ ከድካሙ ነጻ እንዲሆን እንድንማልድለት እንጂ እንድንፈርድ አልተፈቀደልንም፡፡ ሮሜ 14$1፤ 1ዮሐ. 5$16)

ለ. መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ ሆኖ የሚማልደው ጸሎት፡፡ ይሄ ጸሎት መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ሆኖ ነገር ሁሉ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንዲከናወን የሚያቀርበው ጸሎት ነው፡፡

‹‹እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንዲገባን አናውቅምና፣ ነገር ግን መንፈስ ራሱ (እግዚአብሔር) የመንፈስ ሐሳብ ምን እንደሆነ ያውቃል እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና፡፡›› ሮሜ 8$26-27)

ሐ. የምልጃን ጸሎት ማቅረብ የሚችል በሕይወት ያለ ሰው እንጂ የሞቱ ጻድቃንና ሰማዕታት ወይም መላእክት አይደሉም፡፡ መክ. 9$4-6፤ ራዕ. 22$8-9

 

4. የምሥጋና ጸሎት

ይህ ጸሎት ከሌሎቹ ይልቅ ይበልጥ መለማመድ ያለብን የጸሎት ዓይነት ነው፤ ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም ኅብረት የሚኖረን እግዚአብሔርን በምሥጋና በምናመልክበት ጊዜ ነው፡፡

ሁለት ዓይነት የምሥጋና ጸሎት አለ፤

ሀ. እግዚአብሔር ስላደረገልን ነገሮች እግዚአብሔርን ማመስገን፡፡ መዝ. 103$1-5፤

ለ. ስለ እግዚአብሔር ማንነት እግዚአብሔርን ማመስገን፡፡

            መዝ. 117(118)፡1፤ ኢዮ. 1$21፤ 42$2

5. የሥልጣን ጸሎት

ይህ ጸሎት እግዚአብሔር የሰጠንን የልጅነት ሥልጣን ተጠቅመን ሰይጣንን የምንቃወምበት ጸሎት ነው፡፡ ሰይጣንንም የምንቃወመው

ሀ. በኢየሱስ ስም

ለ. በኢየሱስ ደም

ሐ. በእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡

‹‹እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ ዲያብሎስን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል፡፡›› ያዕ. 4$7-8

 

2. የእግዚአብሔር ቃል

አንድ ተክል ከአየር ሌላ ውሃና ማዕድን (ምግብ) እንደሚያስፈልገው ሁሉ፣ አንድ ክርስቲያንም ለማደግ የእግዚአብሔርን ቃል በየዕለቱ መመገብ አለበት፡፡

 ‹‹እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኮልንም ሁሉ ግብዝነትንም ሁሉ ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ፤ ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደሆነ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደተወለዱ ሕፃናት ተንኮል የሌለበትን የቃሉን ወተት ተመኙ፡፡›› 1ጴጥ. 2$1-3

የእግዚአብሔር ቃል በሕይወታችን ሊኖረው የሚገባው ስፍራ

ሀ. ብርሃናችን ነው፡፡ ‹‹ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው፡፡›› (መዝ. 118$105)

ለ. መንገዳችንን ያነጻል፡፡ ‹‹ጐልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል@ ቃልህን በመጠበቅ ነው፡፡›› መዝ. 118$9

ሐ. ሕይወታችንን ያንጻል፡፡ ‹‹አሁንም ለእግዚአብሔርና፣ ያንጻችሁ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ መካከል ርስትን ይሰጣችሁ ዘንድ ለሚችል ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ፡፡›› ሐዋ. 20$32

መ. ከእግዚአብሔር የተሰጠንን መንፈሳዊ ርስት ያሳየናል፡፡ ሐዋ. 20$32 ይህ ርስት የእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች ናቸው፡፡

ሠ. መንፈሳዊ ሰይፋችን ነው፡፡ ‹‹የመንፈስን ሰይፍ ያዙ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡›› ኤፌ. 6$17

ረ. መንፈሳዊ ምግባችን ነው፡፡ ‹‹... አሁን እንደተወለዱ ሕፃናት የቃሉን ወተት ተመኙ፡፡›› 1ጴጥ. 2$1-3

ሰ. እውነትን የምናውቅበት መንገድ ነው፡፡ ‹‹የእውነትን ቃል እርግጥነት አስታውቅህ ዘንድ፣ ለሚጠይቅህም የእውነትን ቃል መመለስ ይቻልህ ዘንድ፣ በምክርና በእውቀት የከበረን ነገር አልጻፍኩልህምን@›› ምሳሌ 22$20-21

እውነት ደግሞ ነፃ ያወጣናል ዮሐ. 8$32፤ ያዕ. 1$25

ሸ. የማስተዋልና የጥበብ ምንጭ ነው፡፡ ‹‹ትእዛዝህ (ቃልህ) ከጠላቶ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ፡፡ ... ካስተማሩኝ ሁሉ ይልቅ አስተዋልኩኝ፡፡ ትእዛዝህን (ቃልህን) ፈልጌአለሁና ከሽማግሌዎች ይልቅ (አስተዋልኩኝ)፡፡›› መዝ. 118$98-100፤ ምሳሌ 1$1-7

ቀ. ከስህተት የምንጠበቅበት መመሪያችን ነው፡፡

‹‹መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ፡፡›› ማቴ. 22$29

በ. ሕይወታችንን የሚያጠራ እሳት ነው፡፡

‹‹በውኑ ቃሌ እንደ እሳት፣ ድንጋዩንም እንደሚያደቅቅ መዶሻ አይደለችምን›› ኤር. 23$29

ተ. የደነደነውን ልባችንን የሚሰብር መዶሻ ነው፡፡ ኤር. 23$29፡፡

ቸ. ልብንና ኩላሊትን (የሰውን የውስጥ አሳብ) የሚመረምር መንፈሳዊ ራጂ (X-ray) ነው፡፡

‹‹የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና የሚሠራም፣ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፤ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፡፡›› ዕብ. 4$12

የእግዚአብሔር ቃል ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች የሚሆንልን ስናነበውና ስንሰማው ብቻ ሳይሆን ሰምተን ሥራ ላይ ስናውለው ነው፡፡

‹‹ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ፡፡›› ያዕ. 1$22-25

 

3. ከአማኞች ጋር ኅብረት ማድረግ፣

አንድ ተክል ከአየርና ከምግብ ሌላ የፀሐይ ብርሃን እንደሚያስፈልገው ሁሉ፤ አንድ አማኝም እውነተኛ ክርስትያኖች ወዳሉበትና የእግዚአብሔር መንፈስ ወደሚሠራበት ስፍራ ከሌሎች አማኞች ጋር ኅብረት ለማድረግ መንገዱን ወደዚያ መቅናት አለበት፡፡ አንዲት ፍም ለብቻዋ ብትሆን በአካባቢው ነፋስ ቶሎ እንደምትከስም እኛም እርስ በርስ ካልተሟሟቅን እንቀዘቅዛለን፡፡

ከሎሎች አማኞች ጋር ኅብረት ማድረግ ያለብን ለምንድነው@

1.     እግዚአብሔር ልዩ የሆነ በረከትን በዚያ ስፍራ ስለሚያፈስ

   ‹‹ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ እነሆ መልካም ነው፣ እነሆም ያማረ ነው፤ ... በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዞአልና፡፡›› መዝ. 133

2.     ጌታ ኢየሱስ በመካከላችን ስለሚገኝ (ማቴ. 18$20)

   እንደውም መሰብሰብ ያለብን ከእርሱ ለመስማትና ለመቀበል እንጂ ሰውን ለማየት መሆን የለበትም፡፡

3.     ፍቅርን ለመስጠትና ለመቀበል፤ ዮሐ. 13$34-35፤ ዕብ. 10$24-25

4.     ለመልካም ሥራ እንድንነቃቃ ኤፌ. 2$10፤ ዕብ. 10$24-25

5.     እርስ በርሳችን እንድንመካከር ዕብ. 10$24-25

6.     በአንድ አካል ውስጥ ብዙ ብልቶች እንዳሉ፣ ነገር ግን ሁሉም በአንድነት አካሉን ለማሳደግ እንደሚሠሩ ሁሉ እኛም እንደ አንድ የክርስቶስ አካል አብረን እንድናድግና እንድንተናነጽ፡፡ 1ቆሮ. 12$31፤ 14$26

ለክርስቶስ መኖር

‹‹ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ ሞትም ጥቅም ነውና›› ፊል. 2$12

በዚህ ጥቅስ ጳውሎስ የሚናገረው፤ በሕይወት ብኖር የምኖረው ለክርስቶስ ነው፤ ብሞትም ወደ ተሻለ ቦታ፤ ወደ እርሱ ስለምሄድ ሞት ለእኔ ጥቅም እንጂ ጉዳ አይደለም ነው፡፡ ክርስቶስን ወደ ሕይወታችን ከተቀበለልን በኋላና በክርስቶስ ማደግ ከጀመርን ለክርስቶስ መኖር አለብን፡፡ በሌላ አነጋገር የምንኖረው የክርስቶስን ፈቃድ ለመፈጸም እንጂ የራሳችንን ወይም የሌሎችን ሰዎች ፈቃድ ለመፈጸም መሆን የለበትም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በሐዋ. 13$36 ስለ ዳዊት ሕይወት ሲናገር ‹‹ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ (ፈቃድ) ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፡፡›› ይላል፡፡ እኛም በሕይወት ዘመናችን ማገልገል ያለብን የእግዚአብሔርን አሳብና ፈቃድ እንደሆነ ያስተምረናል፡፡

ለክርስቶስ የምንኖረው እንዴት ነው@

ለክርስቶስ የምንኖረው ፈቃዱን ስናውቅና ፈቃዱን ሥራ ላይ ስናውል ነው፡፡ ነገር ግን የብዙዎቻችን ጥያቄ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዴት አውቃለሁ የሚል ነው፡፡ እግዚአብሔር እንድናውቅ የሚፈልገውን ፈቃዱን በቃሉ ውስጥ ጽፎልናል፡፡

‹‹የእውነትን ቃል እርግጥነት አስታውቅህ ዘንድ፣ ለሚጠይቅህም እውነትን ቃል መመለስ ይቻልህ ዘንድ በምክርና በእውቀት የከበረን ነገር አልጻፍሁልህምን@›› ምሳሌ 22$20-21

ከቃሉ ዘወር ብለን የጌታን ፈቃድ ማወቅ አንችልም፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል በግል ስናጠናም ሆነ በእግዚአብሔር ቤት ሄደን የእግዚአብሔርን ቃል ስንማር የእግዚአብሔር ፈቃድ የበለጠ እየተገለጸልን ይሄዳል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ከተገለጸልን በኋላ ግን በተገለጸልን ብርሃን መጠን ካልተመላለስን የእግዚአብሔርን ቃል መስማቱና ማንበቡ ብቻ ምንም አይጠቅመንም፡፡

‹‹እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን (ወይም በቃሉ) ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት ለን ጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአ ሁሉ ያነጻናል›› 1ዮሐ. 1$7

ከዚህ ጥቅስ የምንረዳው በብርሃን ወይንም በቃሉ ከተመላለስን ከክርስቶስ ጋር ኅብረት እንደሚኖረን በኃጢአት ብንወድቅ እንኳ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአታችን ሁሉ እንደሚያነጻን ነው፡፡

‹‹ሕግህ (ቃልህ) ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው፡፡›› መዝ. 119$105

እግዚአብሔር በቃሉ ውስጥ የገለጸልንን ሁለት ዐቢይ ፈቃዶች እንመልከት

‹‹ከእነርሱም አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው፣ መምህር ሆይ፣ ከሕግ የትኛይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት@ ብሎ ጠየቀው፡፡ ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህም፣ በፍጹም አሳብህም ውደድ፡፡ ታላቂቱና ፊተኛዪቱ ትእዛዝ ይህች ናት፡፡ ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፣ እርስዋም፣ ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት፡፡ በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም  ነቢያትም ተሰቅለዋል (ተጠቃለዋል)፡፡›› ማቴ. 22$35-40

1. እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችን በፍጹም ሐሳባችን፣ በፍጹም ኃይላችን መወደድ፡፡

 እግዚአብሔርን እንደዚህ ከወደድን እርሱን ደስ የማያሰኝ ነገር አናደርግም፡፡ አድርጉ የሚለንን ነገሮች ሁሉ ደግሞ እያደርጋለን፡፡

‹‹ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ›› ዮሐ. 14$15

‹‹እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንደ በእግዚአብሔር ርኅራሄ እለምናችኋለሁ፣ ይህም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ፡፡›› ሮሜ 12$1-2

2. ራሳችንን እንደምንወደው ሌሎችን መውደድ፡፡ ሰዎችን እንደ ነፍሳችን ከወደድን ክፉ ነገር አናደርግባቸውም፣ ስለ እነርሱ ክፉ አናስብም፡፡ ሰዎች እንዲያደርጉልን የምንመኘውን እኛ እናደርግላቸዋለን፡፡ በተለይም ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ የሚገኘውን የዘላለም ሕይወት ያላገኙ ከሆኑ፤ እንደልይላቸዋለን፣ እንመሰክርላቸዋለን፡፡

              የመመስከር ኃላፊነት አለብን

‹‹እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የለየ ወገን ናችሁ፡፡›› 1ጴጥ. 2$9

በክርስቶስ የምናፍር ከሆነ እርሱም በአባቱ ፊት ያፍርብናል፡፡ ጌታ የምንኮራበትና የምንመካበት እንጂ የሚታፈርበት ጌታ አይደለም፡፡

‹‹በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ፡፡›› ማቴ. 10$32-33

ምስክርነት ምን ማለት ነው@

‹‹ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያ የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውን እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፣ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፡፡›› 1ዮሐ. 1$1-2

ይህ ጥቅስ ምስክርነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ አድርጎ ያስረዳናል፡፡ ምስክርነት ማለት በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል የተገለጠልንንና የተለማመድነውን የዘላለም ሕይወት ለሌሎች መንገር ማለት ነው፡፡ እኛ የተቀበልነውን ሌሎች እንዲቀበሉ መጋበዝ ነው፡፡

ለክርስቶስ የምንመሰክረው እንዴት ነው@

ሀ. በሕይወታችን

‹‹እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፡፡ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም፡፡ መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም፤ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል እንጂ፡፡ በቤት ላሉት ሁሉ ያበራል፡፡ መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ፡፡›› ማቴ. 5$14-16

ሕይወታችን የከርስቶስን ብርሃን የሚያሳይ መሆን አለበት፡፡ ሕይወታችን (አኗኗራችን) ለክርስቶስ የማይመሰክር ከሆነ አንደበታችንም ባይመሰክር ይሻላል፡፡ ምክንያቱም ኑሮአችን ከአንደበታችን የበለጠ ይናገራል፡፡

ለ. በአንደበታችን

‹‹በእናንተ ስላለ ተስፋ ምከንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት (በጥንቃቄ - ጤናማ ወይም ቅዱስ ፍርሃት) ይሁን፡፡››  1ጴጥ. 3$15

ምስክርነታችን በአኗኗራችን ብቻ ሳይሆን በአንደበታችንም መሆን አለበት፡፡ ‹‹እግዚአብሔርን አመስግኑ፣ ስሙንም ጥሩ ለአሕዛብም ሥራውን አውሩ፡፡›› መዝ. 104$1

‹‹የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ... ናችሁ፡፡›› 1ጴጥ. 2$9

በአንደበታችን ስንመሰክር

1.           ጌታ በሕይወታችን የሠራውን ሥራ፣ እንዴት እንደተለወጥን፣ ከምን ዓይነት ሕይወት ወደ ምን ዓይነት ሕይወት እንደተሸጋገርን መናገር፡፡

2.           በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ስለ ሰዎች ኃጢአተኛነትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት የሚናገሩትን ጥቀሶች አጥንተን ለሰዎች መንገር፡፡

‹‹በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፡፡›› ፊል. 2$15

ሀ. እግዚአብሔር እንደሚወዳቸው፤ ዮሐ. 3$16፤ ኤር. 29$11

ለ. ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ እንደሆነና የኃጢአት መጨረሻው የዘላለም ጥፋት እንደሆነ (ሮሜ 3$23፤ ሮሜ 6$23)

ሐ. ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሲል እንደሞተልንና፣ ንሥሐ ገብተን በእርሱ ብናምን የዘላለምን ሕይወት እንደምናገኝ፡፡ ሮሜ 5$8፤ ዮሐ. 3$16፤ ሮሜ 10$9-10፤ ራእ. 3$20

‹‹እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል፡፡›› ማቴ. 24$13